መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጎባ ሪፈራል ሆስፒታል ከቦሳድ( BOSAD) ሃገር አቀፍ የጥናት እና ምርምር ቡድን ‘’BOne Setting Associated Disability’’ ጋር በመሆን ከተለያዩ ወረዳዎች ለተውጣጡ የባህል ህክምና ባለሙያዎች በአጥንት እና መገጣጠሚያ ላይ የሚደርሰው አደጋ ለመቀነስ የአንድ ቀን የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት አካሄደ።
የውይይቱ ዋና አላማ ከአጥንት እና መገጣጠሚያ ጉዳቶች ጋር ተያይዘው የሚመጡ ዉስብስብ የጤና እክሎች የባህላዊ የህክምና ባለሙያዎች በምን መንገድ ከዘመናዊ ህክምና ጋር በማስተሳሰር እና በመተባበር መስራት እንዳለባቸው እና አደጋዉ በሚከሰትበት ወቅት በምን ሁኔታ ችግሩን መፍታት እንዳለባቸው የተሰጠዉ ስልጠና ከፍተኛ ሚና ያለዉ መሆኑን በመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጎባ ሪፈራል ሆስፒታል የአጥንት ህክምና ስፔሻሊስት ሀኪም ዶ/ር ሎጵሶ ሀይለማርያም ገልፀዋል።
አክለውም በሃገራችን በተለምዶ ከሚከሰቱ የአጥንት እና መገጣጠሚያ ጉዳቶች ጋር ተያይዞ በማህበረሰባችን ዘንድ እንደ ግንባር ቀደም የህክምና አማራጭ የሚወሰዱት የባህል ህክምና ልማዶች ጋር ተያየዘው በሚመጡ የተለያዩ ውስብስብ የጤና ችግሮች ለማስቀረትና ለባህላዊ ህክምና ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ከሮቤ ከተማ፣ ጎባ ፣ድንሾ ፣ አጋርፋ፣ ሲናና ወረዳዎች ለተውጣጡ ከሀምሳ በላይ ለሚሆኑ የባህል ህክምና ባለሙያዎች ስልጠና መሰጠቱን ገልፀዋል።
በሌላ በኩል የአጥንት እና መገጣጠሚያ ጉዳቶች በሚከሰቱበት ወቅት የባህላዊ ህክምና ባለሙያዎች ከዘመናዊ ህክምና ባለሙያዎች ጋር ሳይመካከሩ የተጎዳ አካልን አጥብቆ ማሰር እና በድግግሞሽ ማሸት በአንድ ቦታ ረግቶ የተቀመጠና በቀዶ ህክምና መዉጣት የነበረበትን ደም በእሽት ምክንያት ተበጣጥሶ ሊበተን ስለሚችል በቀላሉ ወደ ሌላ የከፋ ጉዳት ስለሚያስከትል ባህላዊ የህክምና ባለሙያዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው የአጥንት እና መገጣጠሚያ ህክምና ስፔሻሊስት እና የስፖርት ጉዳቶች ሰብ ስፔሻሊስት ዶ/ር ዝናዬ ዉዴ ገልፀዋል።
አክለዉም ለሁሉም ታካሚዎች ተገቢ እና የተሟላ ህክምና በመስጠት ሊከሰት የሚችል የአካል መቆረጥ እና ሞትን ለመቀነስ ሁሉም የህክምና ባለሙያ በትጋት መስራት አለባቸው ካሉ በኃላ ለባህላዊ ህክምና ሰጪ ባለሙያዎችም ተገቢ የሆነ የአቅም ግንባታ ስልጠናን በመስጠትና ህሙማኑ ተገቢውን ምርመራ እና ህክምና ማግኘት እንዲችሉ ባህላዊ የህክምና ባለሙያዎችም ታማሚዎችን መምከር እንዳለባቸው ገልፀዋል።
በስልጠናው ላይ የተሳታፉት ከተለያዩ ወረዳዎች የተውጣጡ የባህላዊ ህክምና ባለሙያዎችም እንደገለፁት ከዚህ በፊት በተለምዶ የተለያዩ ስብራቶችን ለመመለስ ቀርከሃ ፣ ካርቶን እንዲሁም የተሰበረው ቦታ እንዲለሰልስ በቅቤና በአብሽ በደንብ በማሸት አጥብቀን በማሰር ስራዉን ስንሰራ የነበረ በመሆኑ ይህ አይነቱ እሽት ለከፋና ለተወሳሰበ ችግር እንደሚያስከትል ካገኙት ስልጠና ላይ የቀሰሙት እዉቀት መሆኑን ገልፀዉ ለወደፊት በአከባቢው ከሚገኙ የጤና ባለሙያዎች ጋር በመመካከር እና በመተጋገዝ እንደሚሰሩም ገልፀዋል።
For More Information Use the following links:
Facebook: https://web.facebook.com/MaddaWalabuUniversityPages/
LinkedIn: https://www.linkedin.com/com.../madda-walabu-university-page
Telegram: https://t.me/Maddawalabubot
X/Twitter: https://x.com/MWU_University
WhatsApp: https://whatsapp.com/channel/0029VbCT1iYKbYMFSfNxOq1U
E-mail: info@mwu.edu.et
Event Gallery










