የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተጣለባቸውን አገራዊ ኃላፊነት በሚገባ ለመወጣትና ትርጉም ያለው ውጤት ለማስመዝገብ በቅንጅት ሊሠሩ ይገባል - ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተጣለባቸውን አገራዊ ኃላፊነት በሚገባ ለመወጣትና ትርጉም ያለው ውጤት ለማስመዝገብ በቅንጅት ሊሠሩ ይገባል - ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)

Mar 12, 2026

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መንግሥትና ሕዝብ የጣለባቸውን አገራዊ ኃላፊነት ለመወጣትና ትርጉም ያለው ውጤት ለማስመዝገብ በቅንጅት ሊሠሩ እንደሚገባ የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ገለጹ።


የትምህርት ሚኒስቴር ለሁለት ቀናት የሚቆይ የ2018 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በቁልፍ ተግባራት ላይ የግማሽ ዓመት የስራ አፈጻጸም ግምገማ በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው።

በዚህ መድረክ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት፣ የሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር)፣ የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)፣ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶችና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።


የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በመድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልእክት፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምርምሮችን በማከናወንና ብቁ ዜጋን በማፍራት ረገድ ያላቸው ሚና የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ተቋማቱ አሁን ካለው ዓለም አቀፋዊ ተለዋዋጭ ሁኔታ ጋር ተወዳዳሪ ሆነው እንዲወጡ በልዩ ትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።

የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ከአመራር እስከ ታችኛው የሥራ ክፍል የተቀናጀ ርብርብ ያስፈልጋል ያሉት ሚኒስትሩ ተቋማቱ ለአገር ዕድገት እያበረከቱ ያሉትን አስተዋጽኦ ይበልጥ እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል።


የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ኮራ ጡሸኔ በበኩላቸው፤ ተቋማቱ በሥራ ባሕልና በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ረገድ መሻሻል ማሳየታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ሥራዎች መሻሻል እያሳዩ መሆኑን ጠቅሰው የትምህርት ተደራሽነትና አካታችነትን ከማረጋገጥ ባለፈ በምርምር ጥራት ላይ በትኩረት እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡

ግምገማው ተቋማቱ ከሚኒስቴሩ ጋር በገቡት ውል መሠረት ያከናወኗቸውን ተግባራት እና ያጋጠሟቸውን ፈተናዎች በጥልቀት ለመለየት ያለመ መሆኑ ተገልጿል።


አዲስ አበባ ፤ የካቲት 30/2018(ኢዜአ)

Event Gallery

Gallery image 1
Gallery image 2
Gallery image 3

Related Articles

View All